21/03/2026
ብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን በኦሮሚያ ክልል 2ኛ ዙር የDDR ትግበራ ጀመረ፤
(መጋቢት 12/2018 ዓ.ም ባቱ ብ/ተ/ኮ) ብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን በኦሮሚያ ክልል የኦነግ ሸኔ የቀድሞ ተዋጊዎችን የጦር መሳሪያ ርክክብ፣ ዲሞቢላይዝ የማድረግና የተሃድሶ ሥልጠና በቡልቡላ ጊዜያዊ የዲሞብላይዜሽን ማዕከል በይፋ ጀምሯል፡፡
መድረኩን የኦሮሞ አባገዳዎች፥ ሃዴ-ሲንቄዎች፥ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች በፀሎት፥ በምርቃትና ለቀድሞ ተዋጊዎቹ መልዕክት በማስተላለፍ አስጀምረዋል።
መድረኩን በንግግር የከፈቱት
የኮሚሽኑ የመልሶ ማቋቋም ዳይሬክተር አቶ ገመዳ አለሚ ከግጭትና ከጦርነት ወጥተው የሰላም አማራጭ የተከተሉ የቀድሞ ተዋጊዎችን አድንቀው ኮሚሽኑ እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ በዋናነት ከኦሮሚያ ክልል መስተዳድርና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በተሃድሶ ሂደት ያለፉ የቀድሞ ተዋጊዎች የሰላምና የልማት ኃይል እንዲሆኑ የማድረግ ሥራ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ከዚህ ቀደም ኮሚሽኑ ከክልሉ ጋር በመተባበር ከ5,300 በላይ የቀድሞ ተዋጊዎችን ደረጃውን በጠበቀ የDDR ሂደት አሳልፎ ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ በማድረጉ አሁን በተሳካ ሁኔታ በአከባቢያቸው ልማትና እድገት ቀጥተኛ ተሳታፊና ተጠቃሚ መሆን ችለዋል። አሁን ደግሞ ከ1,700 በላይ የቀድሞ ተዋጊዎችን በተሟላ የDDR ሂደት አሳልፈን ወደ ተደራጀ ሲቪል ሕይወት እንዲገቡ ይደረጋል ብለዋል።
የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አበበ ለገሰ በበኩላቸው ማንኛውንም የሐሳብ ልዩነት በንግግርና በውይይት መፍታት ይቻላል፡፡ ዘላቂ ሰላም የሚገኘው በጦርነት ሳይሆን ለሰላም እና ለጋራ ተጠቃሚነት በጋራ ሲሰሩ ብቻ ነው ብለዋል።
ግጭትና ጦርነት ምን ያህል ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ እንዳስከተለ እና ሰላምን ለማምጣትና ለማጽናት ምን ያክል ዋጋ እንዳስከፈለን በችግሩ ካለፋችሁበት ከእናንተ በላይ የሚረዳ የለም፡፡ ስለሆነም የተገኘውን አንፃራዊ ሰላም እና ልማት በአስተማማኝ መሠረት ላይ ለማስቀመጥ በትጋትና በጽናት በመስራት የልማት አርዓነታችሁን ለማህበረሰባችሁ ልታሳዩና የበደላችሁትን ሕዝብ በልማትና ሰላም ልትክሱት ይገባል ብለዋል፡፡
መሳሪያ በማስረከብ ብቻ ሰላምን ማጽናት አይቻልም፡፡ ሰላም የሚጸናው አምራች ኃይል የሆናችሁ ወጣቶች ጉልበታችሁን ለስራ በማዘጋጀት ዘላቂ ሰላም ለማምጣትና ሕይወታችሁን ለመለወጥና በሀገር ግንባታ ተሳታፊና ተጠቃሚ ለመሆን ከመንግስት ጎን እንድትቆሙ፤ በተሳሳተ መልኩ በጫካ ያሉ ወንድሞቻችሁንና እህቶቻችሁን ወደ ሰላም እንዲመጡ የበኩላቸውን ሚና እንዲትወጡ በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን እያከናወነ ያለው DDR የጦርነትን አስከፊ ሁኔታ በመለወጥ የቀድሞ ተዋጊዎች ወደ ሰላማዊ መንገድ እንዲመለሱና የክልላችን ሰላምና ልማት እንዲጠናከር ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ጠቅሰው ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
በDDR ሂደት የጦር መሳሪያ ርክክብ፣ ቀድሞ ተዋጊ መሆናቸውን የማረጋገጥ፥ የምዝገባና የተሃድሶ ስልጠና ሂደት ጉብኝት ተከናውኗል፡፡
ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መስተዳድር ከተከያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች የተገኙ የስራ ኃላፊዎች፥ የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን አመራሮችና ባለሙዎች በዝግጅት መርሃ-ግብሩ ላይ ተሳትፈዋል፡፡
ብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን በኦሮሚያ፥ በትግራይ፥ በአፋርና በአማራ ክልሎች እስካሁንh ከ85,400 በላይ የቀድሞ ተዋጊዎች በDDR ሂደት በማሳለፍ ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ እያደረገ መሆኑ ይታወቃል፡፡