24/06/2026
በአርጎባ ብሄረሰብ ልዩ ወረዳ ለ1,600 ተጋላጭ ወገኖች የሚውል 33 ሚሊዮን ብር ድጋፍ የቅድመ ዝግጅት ሥራ ተገምግሟል
መዲና- ሰኔ 17/2018 ዓ.ም(አርጎባ ኮሙኒኬሽን )
በአርጎባ ብሄረሰብ ልዩ ወረዳ ለአደጋ ተጋላጭ የማህበረሰብ ክፍሎች የሚደረገውን ሰብአዊ ድጋፍ በውጤታማነት ለማስፈጸም የ1ኛው ዙር የዩኒሴፍ (UNICEF) የገንዘብ ድጋፍ ፕሮግራም የተጠቃሚዎች ምልመላና የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ግምገማ ተካሂዷል።
በግምገማው የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ እንዲሁም የደቡብ ወሎ ዞን ልዑካን ቡድን ከአርጎባ ወረዳ አብይና ቴክኒክ ኮሚቴዎች ጋር በመሆን በቢሮና በመስክ የተከናወኑ ሥራዎችን በመገምገም የጋራ የሪቪው መድረክ አካሂደዋል።
በፕሮግራሙ በአጠቃላይ 33 ሚሊዮን ብር ለ1,600 አደጋ ተጋላጭ ወገኖች የሚውል ሲሆን፣ ተጠቃሚዎቹ በተቀመጡ መስፈርቶች መሰረት በመጀመሪያና በሁለተኛ ዙር በቀጥታ ተለይተው ተመልምለዋል።
ልዑካን ቡድኑ ከወረዳው የሴቶች፣ ሕጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ባለሙያዎች ጋር በመሆን ባካሄደው የቢሮና የመስክ ምልከታ፣ የቅድመ ዝግጅት ሥራው በተቀመጠው ዓላማና አሰራር መሰረት መከናወኑን አረጋግጧል።
በግምገማው ሂደት የታዩ ጠንካራ ጎኖች ተለይተው የተወደሱ ሲሆን፣ ሊሻሻሉ የሚገባቸው ጉዳዮችም በአስቸኳይ ተስተካክለው ወደ ዋናው የትግበራ ምዕራፍ እንዲገባ አቅጣጫ ተሰጥቷል።
በተጨማሪም ተጠቃሚዎች ስለሚደረግላቸው ድጋፍ፣ የክፍያ ሂደትና ገንዘቡን በተገቢው ዓላማ ለመጠቀም በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው የማስተዋወቅ ሥራዎች መጠናከር እንዳለባቸው ተጠቅሷል።
ልዑካን ቡድኑ ፕሮግራሙ በተሳካ ሁኔታ እንዲደርስ ለአበረከቱት አስተዋፅኦ ለአርጎባ ወረዳ አስተዳደር፣ ለአብይና ቴክኒክ ኮሚቴዎች እንዲሁም ለሴቶች፣ ሕጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ምስጋና አቅርቧል።
የአርጎባ ብሄረሰብ ልዩ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ኑር በበኩላቸው ለተደረገው ሰብአዊ ድጋፍ ምስጋናቸውን ገልጸው፣ በወረዳው አሁንም በርካታ ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ ወገኖች እንዳሉ በማስታወስ፣ መሰል የሰብአዊ ድጋፍ ፕሮግራሞች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።